2 ዩባ
2 ዩባ (60 ዓክልበ. እስከ 15 ዓ.ም. የኖረ) የኑሚዲያ ንጉሥ በኋላም የማውሬታኒያ ንጉሥ ነበረ።
2 ዩባ የኑሚዲያ ንጉሥ 1 ዩባ አንድያ ልጅና ወራሽ ነበረ። እናቱ ማን እንደሆነች አልታወቀም። በ54 ዓክልበ. አባቱ በዩሊዩስ ቄሣር ከተሸነፈ በኋላ ራሱን ገደለ። ያንጊዜ ኑሚዲያ የሮማ መንግሥት ክፍላገር ሆነ።
ዩሊዩስ ቄሣር 2 ዩባን ወደ ሮማ አመጣውና ድሉን ለማክበር በሠልፍ አሠለፈው። በሮማ እየቆየ ልጁ ዩባ ሮማይስጥና ግሪክ ይማር ነበረና የሮማ ዜግነት አገኘ። ለትምህርቱ ትጉህ በመሆኑ ከሮማ ሊቃውንት አንዱ ሆነና እድሜው 20 አመት ሲሆን «የሮማ ሥነ ቅርስ» የተባለ መጽሐፍ ጻፈ። አሳዳጊዎቹ ዩሊዩስ ቄሣርና በኋላ ኦክታውያኑስ (ከዚያ ወደፊት አውግስጦስ ቄሣር የተባለውን ስያሜ የወሰደ) ነበሩ። ዩባ ከኦክታውያኑስ ጋር ሲዘመት የመሪነት ልምምድ አገኘ። በ39 ዓክልበ. በአክቲዩም ውግያ በኦክታውያን አጠገብ ተዋጋ።
በ33 ዓክልበ. አካባቢ አውግስጦስ ዩባን ወደ ኑሚዲያ ዙፋን መለሰው። ኑሚዲያ ግን ለሮማ መንግሥት ተገዥና ታማኝ ሆኖ ማገልገሉ እርግጥኛ ነው። በ27 ዓክልበ. አካባቢ አውግስጦስ ለ2 ክሌዎፓትራ ሰሌኔ በትዳር ሰጠው፣ ትልቅ ጥሎሽንም ጨምሮ ንግሥቱም ሆና ሾማት። ይች የግብጽ ንግሥት 7 ክሌዎፓትራና የሮማ መሪ ማርክ አንቶኒ ልጅ ነበረች። በዚህ ወቅት አውግስጦስ ከኑሚዲያ ወደ ማውሬታኒያ ዙፋን አዛወራቸው።
ዩባና ክሌዎፓትራ በማውሬታኒያ ሲደርሱ ዋና ከተማቸው ቄሣርያ ተባለ (የአሁኑ ሸርሸል፣ አልጄሪያ)።
2 ዩባ የትምህርት፣ ኪነትና ሳይንስ ምርመራ ማዕከል አደረገው። ከዚህ ደግሞ ታላቅ የንግድ ደጋፊ ሆነ። ለውጭ አገር የተላኩት ነገሮች በተለይ ዓሣ፣ ወይን፣ ሉል፣ በለስ፣ እህል፣ የእንጨት እቃ፣ ከዛጎልም አሳ የተለቀመ ሐምራዊ ቅለም ነበሩ። ቲንጊስ (በጂብራልታር ወሽመጥ በሞሮኮ ዳርቻ) ዋና የንግድ ወደብ ሆነ። እንዲሁም አውግስጦስ በጋዲር ላይ (በእስፓንያ በኩል) አለቃ ሆኖ አሾመው።
2 ዩባ እራሱ ብዙ መጽሐፍት ስለ ታሪክ፣ ሥነ ፍጥረት፣ መልክዐ ምድር፣ ስዋሰው፣ ስዕልና ቴያትር በግሪክና በሮማይስጥ ጻፈ። ስለ አረቢያ የጻፈው ጽሑፍ በተለይ በሮማ ይወድድ ነበር። ከጻፋቸው መጽሐፍት ግን ትንሽ ከፊል ብቻ አሁን ይገኛል።
በተጨማሪ 2 ዩባ ወደ ካናሪ ደሴቶችና ወደ ማደይራ ተጓዦችን ላከ። አውሬ ውሾች በካናሪ ደሴቶች ስለ ተገኙ፣ ዩባ ስማቸውን «ካናሪዩስ» ('የውሾቹ' ማለት ነው) አላቸው።
በ13 ዓ.ም. ዩባ ልጁን ቶሌሚን አብሮ እንዲነግሥ አደረገ፤ በ15 አረፈ። ቶሌሚም ለብቻ የማውሬታኒያ ንጉሥ ሆነ።
- Juba II Archived ጁን 27, 2008 at the Wayback Machine king of Mauretania - Dictionary of Greek and Roman Biography and Mythology
- Juba II Encyclopaedia Britannica
- emazighen.com/article.php3?_article=41
- የ2 ዩባ መሐልቆች Archived ኤፕሪል 10, 2008 at the Wayback Machine